EthiopiaNews

የትግራይ ክልልን ለሚቀጥሉት 6 ወራት የሚያስተዳድር የፊዴራል መንግሥት ባለአደራ አስተዳደር መመስረቱ ተገለጸ፡፡

በክልሉ የተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ ተፈጥሮ በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ምርጫ እንዲከናወን ሰራዎችን ይሰራል የተባለው ይህ የፌዴራል መንግሥት ባለአደራ አስተዳደር የተመሰረተው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ መሠረት ነው፡፡

ባለአደራ አስተዳደሩ በክልሉ ውስጥ ተፈጥሮ ያለውን የሰላምና የመረጋጋት ችግር በፍጥነት መፍታት፣ የፈረሱ የመንግሥት መዋቅሮችን መልሶ መዘርጋት እና በጦርነት ምክንያት የተጎዱ መሠረተ ልማቶችን በመጠገን እንዲሁም የተፈናቀሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ወደየቀያቸው እንዲመለሱ ይሰራል ነው የተባለው፡፡

አስተዳደሩ በሚያከናውናቸው ሁሉም ተግባራት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች፣ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት፣ የትግራይ ሕዝብን መሠረታዊ ጥቅሞች መሠረት በማድረግ የሚሰራ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

የዕለት ተዕለት አገልግሎቶች ከማቅረብና ለቀጣይ ምርጫ አስቻይ ሁኔታዎችን ከመፍጠር በዘለለ በሌሎች ጉዳዮች ላይ እንደማይንቀሳቀስ የተገለጸው አስተዳደሩ ከፌዴራል መንግሥት በሚሰጠው አቅጣጫና መመሪያ መሠረት ይሰራልም ነው የተባለው፡፡

የባለአደራ አስተዳደሩ 5 ዋና አስፈጻሚዎችን ያካተተ ሲሆን ከእነዚህም መካከል አሰፋ አብርሃ የአስተዳደር እና የሕዝብ አገልግሎት ዋና አስፈጻሚ፣ ⁠ዶክተር ቴዎድሮስ አረጋይ የኢኮኖሚ እና መልሶ ግንባታ ዋና አስፈጻሚ፣ ⁠ብርዳዴል ጄኔራል ገብረ እግዚአብሔር በየነ የጸጥታና ሰላም ዋና አስፈጻሚ ተደርገው ተሹመዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የትግራይ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ረዳኢ ኃለፎም የፖለቲካ እና ሕዝብ አደረጃጀት ዋና አስፈጻሚ እንዲሁም ⁠ዶክተር ሽሻይ አማረ የመቐለ ከተማ ከንቲባ በመሆን መሾማቸውን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ገልጿል፡፡