EthiopiaNews

የኃይል ደህንነትን ለማጠናከር ያግዛል የተባለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ፕሮግራም ይፋ ተደርጓል፡፡

ፕሮግራሙ ይፋ የሆነው ዛሬ ሁለተኛ ቀኑን በያዘውና በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በተዘጋጀው የውሃና ኢነርጂ ሳምንት መርሃ ግብር ላይ ሲሆን ለሁሉም ዜጎች የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ፣ የኃይል ደህንነትን ለማጠናከርና ኤሌክትሪክን ለአገራዊ የኢኮኖሚ ለውጥ መሠረት ለማድረግ አስተዋፅኦ አለው ተብሏል፡፡

ይፋ የተደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ፕሮግራም የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን አስተማማኝ፣ ተመጣጣኝና ዘላቂ የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ለህዝብ አገልግሎቶች፣ ለኃይል ደህንነትና የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም ለሚችል ዘላቂ ልማት መሠረት የሚጥል ስለመሆኑ ተገልጿል፡፡

ተሳታፊዎቹ የፕሮግራሙን ስትራቴጂያዊ አቅጣጫ፣ የትግበራ ማዕቀፍ፣ የኤሌክትሪክ አውታር መረብ አፈፃፀም፣ የአቅርቦት ዋጋ ተመጣጣኝነት፣ የፋይናንስ ዘላቂነትና የኢንቨስትመንት ማሰባሰብ ላይም እንደሚወያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስታውቋል፡፡

በውይይቱ ላይ የኢነርጂ ሚኒስቴር አመራሮችና ሠራተኞችን ጨምሮ የመንግስት ተቋማት፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አቅራቢዎች፣ የቁጥጥር አካላት፣ የልማት አጋሮች፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ የግሉ ዘርፍ ተወካዮችና ሌሎች ቁልፍ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ እንደሚገኙም ተነግሯል፡፡