የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የታሸጉ ውሀዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ለማቅረብ ከውሀ አምራቾች ማህበር ጋር ስምምነት መደረሱን አስታወቀ።
ቢሮው ይሄን ያለው ከውሀ አቅራቢዎች ማህበር አመራሮች ጋር በመዲናዋ የታሸጉ ውሀዎች በተመጣጣኝ ዋጋ በሚቀርብበት ሁኔታ ላይ ባካሄደው የውይይት መድረክ ነው።
በውይይት መድረኩ ከታሸጉ ውሀዎች አቅርቦት ጋር ተያይዞ ከዋጋና ከጥራት አንፃር የተካሄደ የዳሰሳ ውጤት ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል።
በመድረኩ የውሀ አቅራቢዎች ማህበር አመራሮች የታሸገ ውሀን ከማምረት ጀምሮ በግብይት ሂደት ይታያሉ ያሏቸውን ችግሮች በተለይም የማምረቻ ጥሬ ዕቃ ላይ ያለውን የደላላ ጣልቃ ገብነት አንስተው በመንግስት በኩል መፍትሄ እንዲሰጥበት ጠይቀዋል።
ከውሀ ምርት ጋር በተያያዘ ፋብሪካዎች ለአከፋፋዮችና ለቸርቻሪዎች የሚሸጡበትን ዋጋ በየግላቸው ወስነው በማህበራቸው አማካይነት በአጭር ጊዜ ለአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ለማሳወቅ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።
