የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ችግሮቻቸውን ያለ አሜሪካ ጣልቃ ገብነት መፍታት እንደሚችሉ የኢራኑ ፕሬዝዳንት ገለፁ።
የኢራኑ ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን የመካከለኛው ምስራቅ ቀጣና ችግሮቹን ያለ አሜሪካ ጣልቃ ገብነት መፍታት እንደሚችል ለሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ነግረዋቸዋል ነው የተባለው።
ፕሬዝዳንቱ በሞስኮ በተካሄደው የጋዝ ላኪ ሀገራት መድረክ ጉባዔ ጎን ለጎን ከፑቲን ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ቀጣናው በአሜሪካ ላይ ጥገኛ ሳይሆን በራሱ አቅም ውስጣዊ ችግሮቹን የመፍታት ብቃት እንዳለው እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በበኩላቸው በውይይቱ አሳሳቢ እየሆነ የመጣው የቀጠናው ጦርነት ሁኔታዎች ወደ በጎ አቅጣጫ ይቀየራሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸው አመልክተዋል።
ፑቲን ሁለቱ ሀገራት ጎረቤታሞች መሆናቸውንና በርካታ የጋራ ጥቅሞች እንዳሏቸው ገልጸው፣ እነዚህን ጥቅሞች እውን ለማድረግ በጋራ እየሰሩ እንደሚገኙም አብራርተዋል።
