በጸሃይ ኃይል የሚሠሩ የኃይል ማመንጫዎች አምራች የሆነው የጃፓኑ ቶዮ ኩባንያ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ አምርቶ ወደ አሜሪካ የሚልካቸው ምርቶች ወደ ገበያ እንዲገቡ የሀገሪቱ ጉምሩክ እና ድንበር ጥበቃ ፈቃድ መስጠቱን ገለጸ፡፡
ኩባንያው አክሎም ወደ ሀገሪቱ ልኳቸው የነበሩና በአሜሪካ ጉምሩክ ተይዘው የነበሩ ምርቶቹ እንደተለቀቁለትም አስታወቋል፡፡
ከቻይና መገጣጠሚያዎችን በማስገባት ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ፋብሪካዎቹ በመገጣጠምና ወደ አሜሪካ በመላክ፣ አሜሪካ በቻይና ላይ የጣለችውን ታሪፍ እየተላለፈ ነው በሚል ምርመራ ሲካሄድበት የቆየው ኩባንያው የምርቶቹን የአቅርቦት ሠንሠለት የሚያሳይ ሠነድ አቅርቦ ከተመረመረ በኋላ ምርቶቹ እንደተለቀቁለትም ገልጿል።
የቶዮ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ታካሂኮ ኦኖዙካ በጉዳዩ ላይ በሰጡት መግለጫ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚመረቱ የቴክኖሎጂ ግብዓቶች የአሜሪካን ጥብቅ የጥራት፣ የህግ እና የደህንነት ማጣሪያ አልፈው ወደ ገበያ መግባት መቻላቸውንም ገለጸዋል፡፡
ከፍተኛ የሆነ የግልጽነት እና የህግ አከባበር ደረጃን እንከተላለን ያሉት ስራ አስፈጻሚው ደንበኞች የፀሐይ ኃይል ምርቶቻቸው ከየት እንደሚመጡ እርግጠኛ መሆን እንዳለባቸውና፣ ኩባንያቸውም ሙሉ የአቅርቦት ሰንሰለቱን ግልጽ በማድረግ በአርአያነት እንሰራለንም ነው ያሉት፡፡
