የ2018 የግብር ዘመን የደረጃ “ሀ” ዓመታዊ የንግድ ትርፍ የማሳወቂያና የመክፈያ ጊዜ በመጪው ጥቅምት 30/2019 ዓ.ም የሚጠናቀቅ በመሆኑ ግብር ከፋዮች በወቅቱ ግብራቸውን አሳውቀው እንዲከፍሉ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ጥሪ አቅርቧል።
የደረጃ “ሀ” ግብር ከፋዮችን ዓመታዊ የንግድ ትርፍ ግብር የማሳወቅና የመክፈል ሂደት ሙሉ በሙሉ በኦንላይን እየተካሄደ መሆኑን የገለጸው ቢሮው በዚህም መሰረት ግብር ከፋዮች በአካል ወደ ቢሮ መምጣት ሳያስፈልጋቸው እንዲከፍሉም ጠይቋል፡፡
ግብር ከፋዮች የሂሳብ መዝገቦቻቸውን በሲስተም አማካኝነት በመላክ ሂደቱን ባሉበት ሆነው መከታተል ይችላሉ ያለው ቢሮው የኦዲት ሥራው ተከናውኖ የክፍያ ማዘዣ በሲስተሙ ሲደርሳቸው ክፍያቸውን መፈጸም የሚችሉ መሆኑንም ገልጿል፡፡
ሐምሌ 1 ቀን ጀምሮ እየተካሄደ የሚገኘው የደረጃ “ሀ” ግብር ከፋዮች ግብር የማሳወቅና ክፍያ የመፈጸም ተግባር ጥቅምት 30/2019 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ያሳወቀው ቢሮው ግብር ከፋዮች በመጨረሻዎቹ ቀናት ከሚያጋጥሙ የሲስተም መጨናነቅ፣ ወረፋና መጉላላት እንዲሁም በወቅቱ ባለመክፈል ከሚመጣ ቅጣት ለመዳን በወቅቱ እንዲከፍሉም ማሳሰቢያ ሰጥቷል።
