የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሃረሪ ክልል እና አዲስ አበባን ጨምሮ ከ26 ከተሞች ውጪ በሚገኙ ቅርንጫፎች ሂሳብ የከፈቱ ደንበኞች እስከ ከጥቅምት 30 2019 አ.ም ሂሳባቸውን ከፋይዳ መታወቂያቸው ጋር እንዲያስተሳስሩ አሳሰበ።
ባንኩ ይሄን ያለው ባወጣው አጭር ማስታወቂያ ነው።
በአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ አስተዳደር፣ ባህር ዳር፣ ጎንደር፣ ደሴ፣ ደብረብርሃን፣ ኮምቦልቻ፣ ሀዋሳ፣ አርባ ምንጭ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ሆሳዕና፣ ወራቤ፣ ቡታጂራ፣ ወልቂጤ፣ ሸገር፣ ጅማ፣ አዳማ፣ ሻሸመኔ፣ ቢሾፍቱ፣ ባቱ፣ አምቦ፣ መቐለ፣ አክሱም፣ ዓዲግራት፣ ጋምቤላ፣ አሶሳ እና በሐረሪ ክልል የሚገኙ እና እስካሁን ሂሳባቸውን ከፋይዳ መታወቂያ ጋር ባለማስተሳሰራቸው ምክንያት ሂሳባቸው የታገደ ደንበኞች ሂሳባቸውን ከፋይዳ መታወቂያቸው ጋር በማስተሳሰር በሂሳባቸው ላይ የተጣለውን እገዳ ማንሳት ይችላሉ ተብሏል።
የባንኩ ደንበኞች የፋይዳ መታወቂያ ቁጥራቸውን ይዘው በባንካቹ ቅርንጫፎች በመገኘት ወይም ባሉበት ሆነው በበይነ መረብ ማስተሳሰሪያ አማራጭ (https://cbefayda.cbe.com.et) ሂሳባቸውን ከፋይዳ መታወቂያቸው ጋር ማስተሳሰር እንደሚችሉ ተገልጿል።
የፋይዳ መታወቂያ ያላወጡ ደንበኞች ወደሚቀርባቸው የባንኩ ቅርንጫፎች ማንነታቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ይዘው በመቅረብ መመዝገብ እና የፋይዳ ቁጥራቸውን ማግኘት እንደሚችሉ ተነግሯል።
መረጃው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተገኘ ነው።
