የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ 3 ወራት ባካሄደው የገበያና የፋብሪካ ምርቶች ጥራት ቁጥጥር ሥራ ከደረጃ በታች የሆኑ ከ8 ቶን በላይ ምርቶች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ማስወገዱን ገልጿል፡፡
በተጨማሪም ከ261 ነጥብ 7 ቶን በላይ የሚገመቱ ምርቶች የደረጃ መስፈርቶችን ያላሟሉ፣ የደረጃ ምልክትና የምርት ጥራት ሰርተፊኬት የሌላቸው በመሆናቸው ውሳኔ እስከሚሰጥባቸው ድረስ ለገበያ እንዳይቀርቡ መታገዳቸውን አስታውቋል፡፡
በጥራት ቁጥጥር ሥራው ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ተለይተው በቀጥታ ከተወገዱት ምርቶች መካከል ከ6 ሺህ በላይ ሊትር ፈሳሽ የእቃና የልብስ ማጠቢያ ሳሙና ፣ ከ1 ሺህ 3 መቶ በላይ ኪሎ ግራም ደረቅ የልብስ ሳሙና እንዲሁም ጁሶች ይገኙበታል ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል የጥራት መስፈርት ያላሟሉና ህጋዊ የሰርተፍኬት ማረጋገጫ ሳይኖራቸው ለገበያ ሊቀርቡ ሲሉ የታገዱት ምርቶች ከ2 መቶ ሺህ ኪሎ ግራም በላይ የቤት ክዳን ቆርቆሮ፣ 35 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ የልብስ ሳሙናና 5 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ ሚስማር መሆናቸው ተገልጿል፡፡
