EthiopiaNews

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የደረጃ ሀ ግብር ከፋዮች ከጥቅምት 30 ቀን 2019 ዓ.ም. በኋላ በኦንላይን የሚያቀርቡትን የሂሳብ መዝገብ እንደማይቀበል አስታወቀ።

ቢሮው ይሄን ያለው ባወጣው አጭር መግለጫ ነው።

ቢሮው የደረጃ ሀ ግብር ከፋዮች ዓመታዊ ግብራቸውን ያለቅጣት የሚከፍሉበት ጊዜ ከሐምሌ 1 ቀን 2018 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2019 ዓ.ም. መሆኑን አስታውሶ የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋ ለማድረግ ከ2019 ዓ.ም ጀምሮ በመዲናዋ ዓመታዊ ግብር ክፍያን በኦንላይን እንዲፈፀም ማድረጉን ገልጿል፡፡

በመሆኑም የደረጃ ሀ ግብር ከፋዮች በተዘረጋው የኦንላይን አሠራር በመጠቀም ከጥቅምት 30 ቀን በፊት የሂሳብ መዝገባቸውን በማቅረብ ዓመታዊ ግብራቸውን እንዲከፍሉ አሳስቧል።

ይሁንና በተቀመጠው የጊዜ ገደብ የሂሳብ መዝገባቸውን በማቅረብ የሚጠበቅባቸውን ዓመታዊ የግብር ግዴታ በማይወጡ ግብር ከፋዮች ላይ ቢሮው ባለው መረጃ በመመስረት ዓመታዊ ግብሩን ከነቅጣቱ በመወሰን ክፍያ እንዲፈፀም የሚጠይቅ መሆኑን አሳውቋል።

መረጃው ከአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የተገኘ ነው።