ኢትዮጵያ የነበራትን የጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት መጠን በ59 ነጥብ 21 በመቶ ከፍ በማድረግ 24 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ብር ማድረሷን የብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስቴር ይህን የገለጸው በዛሬው ዕለት የጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ግመታ ማሻሻያን ይፋ ባደረገበት አገራዊ መድረክ ላይ ነው።
በዚሁ ጊዜም አሁን ላይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከአፍሪካ 5ኛ፣ ከሠሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ደግሞ 3ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ግዙፍ ኢኮኖሚ መሆኑን የብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስትሩ በረከት ፍሥሐጽዮን ተናግረዋል።
ቀደም ሲል የሀገሪቱ የጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት መጠን 15 ነጥብ 9 ትሪሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፤ አሁን በተደረገው ወቅታዊ የማሻሻያ ክለሳ ኢኮኖሚው በከፍተኛ ደረጃ ማደጉን አሳይቷል ነው የተባለው።
በአዲሱ የምዘና ውጤት መሠረት የአገልግሎት ዘርፍ 35 ነጥብ 91 በመቶ፣ የግብርና ዘርፍ 33 ነጥብ 57 በመቶ፣ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ዘርፍ 30 ነጥብ 2 በመቶ የኢኮኖሚ ድርሻ መያዛቸውን ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ በበኩላቸው አዲሱ የጂዲፒ ስሌት የኢኮኖሚውን ትክክለኛ ወቅታዊ ገጽታ የሚያሳይ በመሆኑ፣ የመንግሥትን ገቢ፣ ወጪና የበጀት ጉድለት በቅርበት ለመከታተልና የፊስካል እቅዶችን በተሻለ መረጃ ለመቅረጽ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
