የትግራይ ባለአደራ አስተዳደር የትግራይ መልሶ ማቋቋም ተቋም ኤፈርት የቀድሞ ቦርድ አባላትን በማገድ፤ በምትኩ አዳዲስ ጊዜያዊ የቦርድ አባላትን ሾሟል፡፡
ባለአደራ አስተዳደሩ፤ የቀድሞዎቹ የቦርድ አባላት ሕገወጥ ካላቸው አካላት ጋር በመተባበር ድርጅቱን አደጋ ላይ ጥለዋል ያለ ሲሆን እርምጃው የተወሠደው፤ ኩባንያውን ከውድቀት ለማዳን፣ ሠራተኞቹንና ንብረቶቹን ለመጠበቅ እንዲሁም ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ለማስቀጠል ሲባል መሆኑም ተጠቅሷል፡፡
አስተዳደሩ ባወጣው መሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ፣ ሱር ኮንስትራክሽን፣ መስፍን ኢንዳስትሪያል ኢንጂነሪንግ፣ ትራንስ ኢትዮጵያ፣ አልመዳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካና ኢዛና ማዕድን ልማትን ጨምሮ ሌሎች ድርጅቶችን የሚያስተዳድረውን ኤፈርት በጊዜያዊነት እንዲመሩ 5 የቦርድ አባላትን ነው የሾመው፡፡
አዲስ የቦርድ አባል ሆነው የተሾሙት፤ የኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊው ገብረሕይወት ገ/ማርያም፣ የፋይናንስና ሀብት ትብብር ቢሮ ኃላፊ ሓሰና ተክለ፣ የቴክኖሎጂና መገናኛ ቢሮ ኃላፊ ታደለ መንግስቱ፣ የንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ ተናሄ ወርቅዬ እና የፍትሕ ቢሮ ኃላፊ ገብረመድህን ኃይሉ ናቸው።
