የሀገር መከላከያ ሰራዊት በመቐለ ከተማ ያለውን የጸጥታ ሁኔታ የበለጠ ለማጠናከርና የወንጀል እንቅስቃሴዎችን ለመግታት የሚያስችሉ የጸጥታና ደህንነት መመሪያዎች ማውጣቱ ተገልጿል።
ከዛሬ ጥቅምት 27 ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ የሚተገበሩት የደህንነት መመሪያዎቹ ቀደም ሲል ከእስር ቤት በተለያዩ መንገዶች የተለቀቁ ግለሰቦችና የተደራጁ የዝርፊያ ቡድኖች የሚፈጽሟቸው ህገ-ወጥ ተግባራትን ለመከላከል የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡
በዚህም ከምሽቱ 2 ሰዓት እስከ ጧቱ 12 ሰዓት ድረስ ማንኛውም ተሽከርካሪ፣ ሞተር ሳይክል እንዲሁም ከባድ ተሽከርካሪዎች በከተማዋ ውስጥ መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ሆኖም በልዩ ምክንያት በምሽት ወደ ከተማዋ የሚገቡ ሀገር አቋራጭ ከባደ ተሽከርካሪዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ የተገለጸ ሲሆን ማንኛውም ተሽከርካሪ ህጋዊ የሰሌዳ ቁጥር ሳይለጥፍ መንቀሳቀስና ከህግ ውጭ የሆኑ ማናቸውንም ስቲከሮች ለጥፎ መገኘት በህግ የሚያስጠይቅ ይሆናልም ተብሏል።
የጸጥታ አካላት ህጋዊ የፍተሻ ደብዳቤ በማሟላት ከጠዋቱ 12 እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ድረስ ብቻ ፍተሻ ማካሄድ የሚችሉ ሲሆን ከተፈቀደው ሰዓት ውጭ በጸጥታ ስም ህገ-ወጥ ፍተሻ ማካሄድ ክልክል መሆኑም ተጠቅሷል፡፡
በተጨማሪም ህጋዊ ፍቃድ የሌለው የጦር መሳሪያ የያዘ ማንኛውም ግለሰብ፣ በ3 ቀናት የጊዜ ገደብ በፖሊስ ኮሚሽን በኩል ለተቋቋመው ኮሚቴ ያለ ምንም ቅድመ ምርመራ እንዲያስረክብ የተጠየቀ ሲሆን በዚህ ጊዜ ውስጥ የማያሰርክቡ ግለሰቦች ላይ ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል።
ሁሉም የጸጥታ አካላት መመሪያዎቹን በህጉ መሰረትና በከፍተኛ ኃላፊነት ስሜት እንዲያስፈጽሙ መታዘዛቸውን የክልሉ ቴሌቪዥን ዘግቧል።
