የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ለዘጠነኛ ዙር የመሬት ሊዝ ጨረታ 127 ፕሎቶችን በስምንት ክፍለ ከተሞች ማዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡
ቢሮው ይሄን ያለው ባወጣው መግለጫ ነው።
ቢሮው የሰነድ ሽያጩ ከጥቅምት 30/2019 ዓ.ም እስከ ህዳር 11 2019 አ.ም ባሉት 10 ተከታታይ የስራ ቀናት በኦንላይን እንደሚካሄድ ገልጿል።
የሰነድ ሽያጩም ለዚሁ ዓላማ ተብሎ በተዘጋጀው በዚህ ድረገፅ Website:addislandfarm.gov.et:(https://addislandfarm.gov.et/land-auction) ማግኘት ይቻላል ተብሏል።
የጨረታ ኮሚቴ አስተባባሪ ክብሮም አሰፋ ቢሮው የከተማዋን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማጠናከርና ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት 127 ፕሎቶችን በግልፅ የመሬት ሊዝ ጨረታ አወዳድሮ ለማስተላለፍ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ሙሉ ለሙሉ አጠናቋል ብለዋል፡፡
ጨረታውን ከብልሹ አሰራር ለማላቀቅ ለመጀመሪያ ጊዜ ሂደቱን መሉ ለሙሉ ዲጅታላይዝ ማድረግ መቻሉን የጠቆሙት አስተባባሪው ፤ከፕላን ተቃርኖና ከይገባኛል ነፃ የሆኑ 127 ፕሎቶች ፤ በቦሌ ፣ የካ ፣ አራዳ ፣ ለሚኩራ ፣ ጉለሌ ፣ ኮልፌ ቀራንዮ ፣አቃቂ ቃሊቲ እና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች ለመኖሪያና ለንግድ አገልግሎቶች በሊዝ ጨረታ አወዳደሮ ለማስተላለፍ ዝግጁ አድርጓል ብለዋል፡፡
በጨረታው መሳተፍ የሚፈልግ አልሚ የቦታውን ዝርዝር መረጃ ነገ ቅዳሜ ጥቅምት 28/2019 ዓ.ም ታትሞ በሚወጣው አዲስ ልሳን ጋዜጣ መመልከት እንደሚቻል የቢሮው መረጃ ያሳያል፡፡
መረጃው ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ የተገኘ ነው።
