ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የምታደርገው ድርድር ወደ ወሳኝ ምዕራፍ መሸጋገሩን ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል።
ይህ የተባለው የዓለም ንግድ ድርጅት 8ኛውን የሥራ ቡድን ስብሰባዉን በጄኔቫ፣ ስዊዘርላንድ እያካሄደ ባለበት ወቅት ሲሆን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር እና የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ሂደቱ ዋና ተደራዳሪ ያስሚን ወሀብረቢ የተመራው የልዑካን ቡድን በስብሰባዉ እየተሳተፈ ይገኛል።
ሚኒስትሯ በመክፈቻ ንግግራቸው የድርጅቱ አባልነት ኢትዮጵያ እያካሄደችው ያለው የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር አካል ነው ብለዋል፡፡
በመድረኩ ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል መሆኗ የፖሊሲ ቀጣይነትን እና ግልጸኝነትን ከማጠናከሩም በላይ፣ ምርትና ምርታማነትን፣ የውጭ ንግድን እና ኢንቨስትመንትን በማስፋት የሥራ ዕድልን ለመፍጠር አስተዋጽኦው ከፍተኛ መሆኑ ተገልጿል።
ከባለብዙ ወገን ስብሰባው ጎን ለጎን፣ የሁለትዮሽ የገበያ ዕድል ድርድር ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ሲካሄድ ከሁለቱም ወገኖች ጋር የተካሄደው ድርድር እጅግ ፍሬያማ እንደነበር የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
እስካሁን ለሁለትዮሽ ድርድር የጠየቁ 17 ሀገራት ሲሆኑ ከ11 ሀገራት ጋር ስምምነት ተፈርሟልም ነው የተባለው።
የድርድር ቡድኑ ቀሪ ባለብዙ ወገን ጉዳዮችን በውይይት ለመፍታት ዝግጁ መሆኑም ተጠቁሟል።
