ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የአየር ንብረት ቀውስና የጂኦፖለቲካ ውጥረቶች አለም አቀፍ ትብብርን እየፈተኑ መሆናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ተመራጭ ፕሬዚዳንት ጌዲዮን ጢሞቴዎስ አስታወቁ።
ሚኒስትሩ በቱርክ አንታሊያ እየተካሄደ በሚገኘው 31ኛው የዓለም አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን በንግግራቸውም የቴክኖሎጂ፣ የኢንቨስትመንትና የንግድ ውድድር የአየር ንብረት እርምጃዎችን እየተፈታተነ መሆኑን ገልጸዋል።
የሳይንስ ምሁራዊ ግምገማዎች የማስተካከያ ክፍተቶችን ለመዝጋትና የማይመለሱ ጉዳቶችን ለመቋቋም ፈጣን ምላሽ እንደሚጠይቁ ያነሱት ሚኒስትሩ ኮፕ 31 በማስተካከያ፣ በፋይናንስ፣ ፍትህ ባለው ሽግግር እና በአፈፃፀም ዙሪያ ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ እንዳለበትም አሳስበዋል።
አያይዘውም ለሚቀጥለው የኮፕ 32 ፕሬዚዳንትነት ዋናው ትኩረት በባለብዙ ወገን የአየር ንብረት ትብብር ላይ እምነትን መልሶ መገንባት መሆኑን ጠቁመው ይህ እምነት የሚገኘው በተግባር፣ አካታች በሆኑ ሂደቶች፣ ልዩነቶችን በቁም ነገር በመያዝ እና ዓለም አቀፍ ምኞትን ከሀገራዊ አፈፃፀም ጋር በማገናኘት ጭምር መሆኑን አስገንዘበዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም ግባችን የአየር ንብረት ትብብርን የላቀ ዓለም አቀፍ ትስስር ማጠናከሪያ ምንጭ ማድረግ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
