በጣሊያን፣ ስኮትላንድ እና ሰሜን አየርላንድ ለሚገኙ ከሰባት ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች የሐሰት የቦምብ ስጋት ማስጠንቀቅያ መላኩ ተሰምቷል።
በጣሊያን 6 ሺህ 300 ትምህርት ቤቶች ሃሰተኛው ማስጠንቀቂያ የደረሳቸው ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ግን ምንም ተጨባጭ የአደጋ ስጋት ማስረጃ አለመገኘቱን ገልጸዋል።
የጣሊያን ትምህርት ሚኒስቴር፣ ድርጊቱ በአውሮፓ አየር መንገዶችና ሆስፒታሎች ላይ የተሰነዘረውን ሽብር የሚመስል የሳይበር ጥቃት ነው ብሏል።
በስኮትላንድ እና ሰሜን አየርላንድ ከ700 በላይ ትምህርት ቤቶች ተመሳሳይ የሃሰት የማስጠንቀቂያ መልዕክት የደረሳቸው ሲሆን፤ የሳይበር ወንጀል መርማሪዎች ምንጩን እያጣሩ ይገኛሉ።
በሶስቱ አገራት ለጥንቃቄ ሲባል ተማሪዎች እንዲወጡ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም፤ ስጋቱ ሐሰተኛ መሆኑ ሲረጋገጥ በርካታ ትምህርት ቤቶች መደበኛ ትምህርታቸውን እየቀጠሉ መሆናቸው ተመልክቷል።
