InternationalNews

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ  በእስያ የሚያደርጉትን የአራት ቀናት ቆይታ ለመጀመር ዛሬ ወደ ፊሊፒንስ ያቀናሉ።

ፕሬዝዳንቱ ከሀገራቸው የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ውጤት ማጣት በኋላ በሚያደርጉት በዚህ ጉዞ፣ በፍሊፒንስና ቻይና በሚካሄዱ ጉባኤዎች ላይ እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

ትራምፕ ከነገ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በፍሊፒንሷ ማኒላ ከተማ በሚካሄደው የደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት ጉባኤ ላይ የሚሳተፉ ሲሆን፤ ከመጪው ረቡዕ ጀምሮ በቻይናዋ የቴክኖሎጂ ከተማ ሺንዘን በሚካሄደው የእስያ ፓስፊክ ሀገራት የኢኮኖሚ ትብብር ጉባኤ ላይም እንደሚገኙ ይጠበቃል።

ትራምፕ በዚሁ የእስያ ቆይታቸው ከቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ዢን ፒንግ እና ከሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር ሰፋ ያለ ውይይት እንደሚያደርጉም ተነግሯል።

የሦስቱ መሪዎች ውይይት የኒውክሌር መሳሪያ ቁጥጥርን የተመለከተ አጀንዳን እንደሚያካትት ቅድመ ግምቱን ያስቀመጠው ሮይተርስ፤ ትራምፕ ይህን ውይይት በጥብቅ እንደሚፈልጉት ጠቁሟል።

ፕሬዝዳንቱ፤ ቻይናና ሩሲያ የሰሜን ኮሪያውን ፕሬዝዳንት ኪም ጆንግ ኡንን አሳምነው በቀጣይ ውይይቶች ወደ ጠረጴዛ እንዲያመጧቸው እንደሚፈልጉ ተዘግቧል።

ትራምፕ በእስያ በሚኖራቸው ቆይታ ከሌሎች ሀገራት መሪዎች ጋር ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በዘገባቸው ጠቁመዋል።