EthiopiaNews

የኢትዮጵያ ፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በ2026 የክላይሜት ስካነር ኢምፓክት ሽልማት ‹‹ለተቋማዊ አሠራር መጎልበት ያለው ቁርጠኝነት» በተሰኘው ዘርፍ አሸናፊ መሆኑ ተገለጸ።

መሥሪያ ቤቱ ይህንን ዓለም አቀፍ እውቅና ሊያገኝ የቻለው በአየር ንብረት ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል ዙሪያ የሚከናወኑ ሥራዎችን በኦዲት ሂደት በመከታተል፣ መረጃዎችን በማሰባሰብና በመተንተን በማስረጃ የተደገፉ ሪፖርቶችን ማቅረብ በመቻሉ ነው ተብሏል።

በተቋማዊ አሠራርም መሥሪያ ቤቱ ራሱን የቻለ የአካባቢ ክዋኔ ኦዲት ዳይሬክቶሬት በማቋቋም፣ የአየር ንብረት ለውጥን የሚመለከት ኦዲትን በ2026–2031 ስትራቴጂክ ዕቅዱ ውስጥ ማካተቱ ተነግሯል።

በተጨማሪም የዘላቂ ልማት ግቦን የክዋኔ ኦዲት ማኑዋልን በመተግበር፣ የአየር ንብረት ጥበቃ ሥራዎችንና የሚመዘገቡ ለውጦችን በየጊዜው በኦዲት እንዲገመገሙ አድርጓል ተብሏል።

ሽልማቱ በተለያዩ አገራት ከሚገኙ የዋና ኦዲት ተቋማትና አጋር አካላት በተውጣጣ ዓለም አቀፍ የዳኞች ቡድን የተመረጠ ሲሆን፣ ባሳለፍነው ሳምንት በብራዚል ሪዮ ዴ ጄኔሮ በተካሄደው የክላይሜት ስካነር ጉባኤ ላይ በተዘጋጀው ልዩ የሽልማት ሥነ ሥርዓት ይፋ መሆኑ ተጠቁሟል።