የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልኡካን ከዛሬ ኅዳር 8 ጀምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆይ የሥራ ጉብኝት በመቐለ ከተማ እያካሄዱ መሆኑ ተነግሯል፡፡
ለዚህም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዑካንና የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች መቐለ መግባታቸው ተገልጿል፡፡
ልዑካኑ ከትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች፣ ከሐይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ውይይት እንደሚያደርጉም ተነግሯል።
የትግራይ ክልል ባለ አደራ የአስተዳደር እና የሕዝብ አገልግሎት ዋና አስፈጻሚ አሰፋ አብርሃ ክልሉ ያለበትን አሁናዊ ሁኔታ እና የሚያስፈልጉ ድጋፎችን በተመለከተ ለልዑካኑ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በጦርነቱ በትግራይ ክልል የተከሰተው የተወሳሰበ ችግር ዓለም አቀፉን የተጠናከረ ድጋፍ እንደሚፈልግ አንስተዋል።
ልኡካኑ የሰብአዊ ዕርዳታ፣ ተፈናቃዮች፣ የትጥቅ የማስፈታትና የመልሶ ማቋቋም ሂደትን እንዲሁም የክልሉ ሰላም ጉዳይ ላይ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎም ይጠበቃል።
