የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአራት ወራት ብቻ 2 ሺህ 472 ኪ.ሜ በላይ የኤሌክትሪክ መስመሮችን የመልሶ ግንባታና የማስፋፊያ ሥራ ማከናወኑን አስታወቀ።
ተቋሙ ይሄን ያለው ለጣቢያችን ኢቤኤስ ቴሌቪዥን በላከው መግለጫ ነው።
ሥራዎቹም በተቋሙ የውስጥ ፋይናንስ ብቻ የተከናወኑ መሆናቸው ተገልጿል።
በነባር መስመሮች ላይ በተከናወነው የመልሶ ግንባታና የማሻሻያ ሥራ 749 ኪ.ሜ መካከለኛ መስመር እና 82 ኪ.ሜ ዝቅተኛ መስመር፣ በድምሩ 831 ኪ.ሜ ሥራ ተከናውኗል ተብሏል።
በተጨማሪም ከአቅማቸው በላይ በጭነት ምክንያት የአገልግሎት መቆራረጥ ሊያስከትሉ የሚችሉ 481 ትራንስፎርመሮች በከፍተኛ አቅም ባላቸው ትራንስፎርመሮች ተተክተዋል።
ተቋሙ 411 ተጨማሪ ትራንስፎርመሮች በተለያዩ አካባቢዎች ተከላ እንደተደረገላቸው ገልፆ በእነዚህ የማስፋፊያ ሥራዎች በአጠቃላይ 1 ሺህ 744 ትራንስፎርመሮችም ተከላ ተደርጎላቸዋል ብሏል።
የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሽፋንን ለማስፋፋት በተከናወነው ሥራ ደግሞ 978 ኪ.ሜ መካከለኛ መስመር እና 662 ኪ.ሜ ዝቅተኛ መስመር፣ በድምሩ 1 ሺህ 641 ኪ.ሜ አዲስ መስመር ተዘርግቷል።
