የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከትሬድማርክ አፍሪካ ጋር በመተባበር የ2026 የአፍሪካ ንግድ ልማት ፎረምን በመጪው ሰኞ እና ማክሰኞ ህዳር 14 እና 15 ቀን 2019 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚያካሂድ አስታወቀ።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ያስሚን ወሀብረቢ በሰጡት መግለጫ የፎረሙ ዋነኛ ዓላማ በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ውስጥ ምርቶች ያለእንቅፋት እንዲዘዋወሩ የጥራት ደረጃዎችን ማጣጣምና የጋራ እውቅና ስምምነቶችን መፍጠር ላይ መምከር መሆኑን ገልጸዋል።
እንዲሁም ላቦራቶሪዎችንና የምርት ፍተሻ ስርዓቶችን በማዘመን ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች፣ ወጣቶችና ሴቶች ወደ ውጭ ንግድ የሚገቡበትን እድል ለማስፋት ያለመ ሲሆን፣ አህጉራዊ የቃል ኪዳን ሰነዶችም ይፈረሙበታል ተብሏል።
በመድረኩ የቢዝነስ ለቢዝነስ ትስስሮችንና ስምምነቶችን የሚፈጥሩ ኤግዚቢሽኖችና የፓናል ውይይቶች ይካሄዳሉ የተባለ ሲሆን ከተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅትና ከትሬድማርክ አፍሪካ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ አህጉራዊ ሪፖርትም በፎረሙ ይፋ እንደሚደረግ ተገልጿል።
በዚህ ጉባኤ ላይ የአፍሪካ ሀገራት የንግድ ሚኒስትሮች፣ የአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች እንዲሁም የንግድ ኃላፊዎችን ጨምሮ ወደ 300 የሚጠጉ ተሳታፊዎች ይታደማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተጠቁሟል።
