የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለፈው ጥቅምት ወር ብቻ 66 ሺህ 473 አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስታወቀ።
ተቋሙ ይሄን ያለው ለጣቢያችን ኢቢኤስ ቴሌቪዥን በላከው መግለጫ ነው።
ተቋሙ በወሩ 88 ሺህ 253 አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ ዕቅድ ይዞ የነበረ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 66 ሺህ 473 ደንበኞችን በማገናኘት የዕቅዱን 75.3 በመቶ ማሳካት እንደቻለ ገልጿል።
የወሩ አፈጻጸም ከ2018 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 20 ሺህ 23 ተጨማሪ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ያሳያል።
በወሩ አዲስ ከኤሌክትሪክ መረብ ከተገናኙት ደንበኞች መካከል 62 ሺህ 574 (94.1 በመቶ) የቅድመ ክፍያ ቆጣሪዎች፣ ቀሪዎቹ 3 ሺህ 899 (5.9 በመቶ) ደግሞ የድኅረ ክፍያ ቆጣሪዎች ተገጥመውላቸዋል ተብሏል።
ከጠቅላላው አዲስ ደንበኞች ውስጥ 92 ነጥብ 3 በመቶ በኦፖሬሽን የተስተናገዱ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ 7 ነጥብ 7 በመቶ ደንበኞች ደግሞ በፕሮጀክት አማካኝነት አገልግሎቱን አግኝተዋል።
በዚህም መሠረት እስከ 2019 በጀት ዓመት ጥቅምት ወር መጨረሻ ድረስ የተቋሙ አጠቃላይ ደንበኞች ብዛት 6 ሚሊዮን 90 ሺህ 965 መድረሱን ነው ተቋሙ የገለፀው።
