የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ፣ ዶናልድ ትራምፕ የሩሲያውን ፕሬዝዳንት ፑቲንን ‘’ጓደኛዬ’’ ብለው መጥራታቸውን እንግዳ ነገር ሲሉ በመተቸት የፀረ-ባሊስቲክ ሚሳኤል አቅርቦት መዘግየት የዩክሬናዊያንን ህይወት እያስከፈለ መሆኑን ገለጹ።
ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ፑቲን ወራሪ እና ገዳይ በመሆናቸው ጓደኛ ሊሆኑ እንደማይችሉ ጠቅሰው አሜሪካ በሰላም ድርድሩ በሩሲያ ላይ በቂ ጫና እያሳደረች አይደለም ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
ትራምፕ ከፑቲን ጋር ተቃቅፈው የተነሱትን ፎቶ መለጠፋቸውን የተቹት ዘሌንስኪ፣ በአጥቂው እና በተጠቂው መካከል ገለልተኛ ለመሆን መሞከር አጥቂውን እንደመደገፍ ይቆጠራል ሲሉ ተናግረዋል።
በተጨማሪም የሩሲያ የባሊስቲክ ሚሳኤል ጥቃቶች እየተባባሱ ባሉበት በዚህ ወቅት፣ አሜሪካ የፓትሪዮት የአየር መከላከያ ሚሳኤሎችን አቅርቦት አዘግይታ ትኩረቷን ወደ መካከለኛው ምስራቅ ማድረጓ በዩክሬን ላይ ከፍተኛ የመከላከያ እጥረት መፍጠሩን አስታውቀዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ዩክሬን በሊቢያ ወደብ በሩሲያ የጦር መርከብ ላይ የፈጸመችው ጥቃት ጦርነቱን ወደ ሜዲትራኒያን ባህር ሊያስፋፋ ይችላል ሲሉ ሲተቹ፣ ዘሌንስኪ ግን መርከቧ ትክክለኛ ወታደራዊ ኢላማ ነበረች ሲሉ እርምጃውን ተገቢ ነው ብልዋል።
