EthiopiaNews

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ እጩ መልማይ ኮሚቴ ወይዘሮ ሜላተወርቅ ሃይሉ አበባውንና አቶ ታደሰ ለማ ገርቢን ለቦርዱ ሰብሳቢነት እጩ አድርጎ መምረጡን አስታወቀ።

ኮሚቴው በተቀመጠው የመጠቆሚያ ቅጽ መሰረት 56 ሰዎችን መቀበሉን የገለጸ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 5 ያህሉን መለየቱንና ከ5ቱም 2 ሰዎችን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለማቅረብ መወሰኑን ነው ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠው መግለጫ የተናገረው።

ከተመረጡ እጩዎች ውስጥ በቀዳሚነት የተቀመጡት ወይዘሮ ሜላተወርቅ ሃይሉ አበባው ከዚህ ቀደም በተለያዩ መስሪያ ቤቶች ሲያገለግሉ እንደነበርና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውስጥም የጽ/ቤት ሃላፊ ሆነው ለ2 ዓመታት ያገለገሉ መሆናቸው ተነግሯል፡፡

በሁለተኛ እጩነት የተመረጡት አቶ ታደሰ ለማ ገርቢም በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ምርጫ ክልልን በሃላፊነት ሲመሩ የቆዩ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡

የልየታ ሂደቱ ጥንቃቄ የተደረገበት መሆኑን የጠቀሰው ኮሚቴው የተመረጡት ሰዎች ፍቃደኝነታቸው ተጠይቆ መቅረባቸውን ጠቁሟል።

በመስፈርቶቹ መሰረት ኢትዮጵያዊ መሆናቸው ፣የፖለቲካ ገለልተኝነታቸው፣ በስነምግባራቸው አንቱታን ያተረፉ መሆናቸው፣ ተዓማኒነታቸውና የትምህርት ዝግጅታቸው መታየቱንም ኮሚቴው ገልጿል ።