በኢትዮጵያ የሚገኙ የስኳር፣ የወረቀትና የወረቀት ጥሬ እቃ ፋብሪካዎች እንዲሁም የማዕድን ኮርፖሬሽን አሁንም በኪሳራ ላይ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ አስታውቋል፡፡
የተቋሙ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ያስሚን ወሀብረቢ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት የስኳር ፋብሪካዎች በ2014 በጀት ዓመት 5 ቢሊየን ብር ኪሳራ ያስመዘገቡ ሲሆን በ2015 በጀት ዓመት ግን ወደ ግማሽ ቢሊየን ማውረድ ተችሏል ነው ያሉት።
በሌላ በኩል የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በሩብ ዓመቱ ከ249 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸው የተገለጸ ሲሆን ገቢው ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት አንጻር የ43 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኢትዮ-ቴሌኮም፣ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ እንዲሁም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለገቢው የላቀ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ድርጅቶች መሆናቸውንም ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የሚያስተዳድራቸው ኩባንያዎች አጠቃላይ ብት ከ2 ነጥብ 4 ትሪሊዮን ብር በላይ መድረሱ እንደታወቀም ዘገባው አክሎ አመልክቷል።