EthiopiaNews

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በ2018 በጀት ዓመት ለ52 የመገናኛ ብዙኃን ፈቃድ መስጠቱን አስታወቀ።

ባለሥልጣኑ ይሄን ያለው በ2019 በጀት አመት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎችን አስመልክቶ ባካሄደው የውይይት መድረክ ላይ ሲሆን በህጋዊ መንገድ ፈቃድ ወስደው የሚንቀሳቀሱ ሚዲያዎች ቁጥር 329 መድረሳቸውም ነው የተገለጸው።

ባለሥልጣኑ በ2018 በጀት አመት ለ14 የበየነ መረብ ሚዲያዎች የምዝገባ ምስክር ወረቀት ፈቃድ፣ ለ5 የማህበረሰብ ብሮድካስት ሚዲያዎች ፈቃድ፣ ለ19 የሚዲያ ፕሮግራም አዘጋጆችና ለ9 የማስታወቂያ አዘጋጆች የብቃት ማረጋገጫ መስጠቱን ገልጿል።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሃይማኖት ዘለቀ በሰጡት ማብራሪያ በተጠናቀቀው በጀት አመት ከውጭ ሚዲያዎች ጋር በተያያዘ ለ5 ቋሚ የዜና ወኪሎች ፈቃድ ተሰጥቷል ብለዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም በበጀት አመቱ ከተለያዩ የውጭ አገራት ለአጭር ጊዜ የፊልም ቀረፃና ዘገባ ወደ ወደ ኢትዮጵያ ለመጡ 78 የውጭ ጋዜጠኞችና ዘጋቢዎችም ፈቃድ መሰጠቱን ተናግረዋል። መረጃው ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የተገኘ ነው