EthiopiaNews

የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሁለት ተጨማሪ የሥራ ቡድኖች በተመካከሩባቸው ምክረ-ሃሳቦች ላይ መግባባት ላይ መድረሳቸውን አስታወቀ።

ሁለቱ የስራ ቡድኖች ከመግባባት የደረሱባቸው አጀንዳዎች የመንግሥት አደረጃጀትና ቅርጽ እንዲሁም የፖለቲካ ሥርዓት፣የፖለቲካ ውክልና እና የምርጫ ስርአት እና የሙስና እና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ናቸው ተብሏል።

በእነዚሁ ሁለት አጀንዳዎች ላይ ሲመካከሩ የቆዩት እያንዳንዳቸው 500 አባላት ያሏቸው የሥራ ቡድኖች ተጠናቅረው በቀረቡ የአጀንዳ ምክረ-ሀሳቦች ላይ መግባባት ላይ መድረሳቸውን በተዘጋጁት የቃለ-ጉባኤ ሰነዶች ላይ በመፈረም ማረጋገጣቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል።

ምክክር እየተደረገባቸው ከሚገኙ 8 አጀንዳዎች መካከል እነዚህ ሁለት ተመካካሪ ቡድኖች ተጠቃሽ ሲሆኑ በእነዚህ አጀንዳዎች ላይ በተለያዩ የቡድን አደረጃጀቶችና እርከኖች ሲመካከሩ መቆይታቸው የሚታወስ ነው።

የሌሎች አጀንዳዎች ተመካካሪዎችም በቀጣይ ቀናት በተመሳሳይ መልኩ የአጀንዳ ሃሳቦቻቸውን የጋራ አድርገው በቃለ ጉባኤዎቻቸው ላይ በመፈራረም እንደሚስማሙ ይጠበቃል፡፡መረጃው ከኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተገኘ ነው።