የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ ለሁለተኛ ተከታታይ ዓመት የዓመቱ ምርጥ የባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሽልማትን ማሸነፋቸውን ባንኩ አስታውቋል።
የባንኩ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ የዓመቱ ምርጥ የባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሽልማትን ያሸነፉት በፋይናንስ ዘርፍ ባሳዩት የላቀ አመራር እንደሆነ ባንኩ ገልጿል።
ሽልማቱ የተበረከተው ዓለም አቀፉ የስትራቴጂክ ጥምረት ማዕከል በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል ባካሄደው “29ኛው የኮኔክትድ ባንኪንግ ሰሚት ኢኖቬሽን ኤንድ ኤክሰለንስ አዋርድ 2026” በተባለ መድረክ ላይ ነው።
ፕሬዚዳንቱ አቤ ሳኖ በፋይናንስ ዘርፍ ባሳዩት የላቀ አመራር፣ በተለይም የባንኩን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንና የፈጠራ ጉዞ በበላይነት ለመምራት ላበረከቱት የላቀ አስተዋፅኦ የተሰጠ መሆኑ ተገልጿል።
የባንኩ ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አልሰን አሰፋ ፕሬዚዳንቱን በመወከል ሽልማቱን ከተቀበሉ በኋላ፣ “ይህ እውቅና የባንኩን ጠንካራ አመራር የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ፣ ለመላው የባንኩ ሠራተኞችና ደንበኞች የተበረከተ የጋራ ስኬት ነው” ብለዋል።መረጃው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተገኘ ነው።
