EthiopiaNews

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ አብን የሃገራዊ ምክክር ጉባኤ ሂደቱን አካታችነትና አሳታፊነት በተመለከተ ያወጣውን የቅሬታ መግለጫ ተከትሎ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጉባዔው ነፃና ገለልተኛ በሆነ የአሰራር ሥርዓት እየተመራ ነው የሚል ምላሽ ሰጥቷል።

ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ አብን ሂደቱ አካታችና አሳታፊ አይደለም በማለት ያቀረበውን አቋም መመርመርና ማጣራቱን ጠቅሶ የፓርቲውን ድምዳሜ አልጋራውም ነው ያለው፡፡

ኮሚሽኑ የምክክር ጉባዔው ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሕብረተሰብ ክፍሎች፣ ከመንግሥት አካላትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት የተወከሉ ልዩ ልዩ ድምፆች እየተሳተፉበት መሆኑንም ጠቁሟል።

ከአብንም ሆነ ከሌሎች ወገኖች የሚቀርቡ ቅሬታዎችን በቅሬታ አፈታት ሥርዓቱ መሠረት ምላሽ እየሰጠ እንደሚገኝ የተናገረው ኮሚሽኑ ገንቢ አስተያየቶችን በግብዓትነት ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑን በመግለጫው ጠቁሟል።