ኢትዮጵያ 180 ሺህ ኪሎ ሜትር የመንገድ ሽፋን በመዘርጋት በአፍሪካ ሦስተኛ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ 30ኛ ደረጃን መያዟ ተገለጸ፡፡
መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው ግሎባል ፋየር ፓወር የተሰኘው የመረጃ ተቋም ይፋ ባደረገው የ2026 ሪፖርት ይህንን ያስታወቀ ሲሆን በኢትዮጵያ ያለው የመንገድ ሽፋን እየጨመረ መሆኑንም ነው የጠቆመው፡፡
ኢትዮጵያ በ750 ሺህ ኪሎ ሜትር የአፍሪካን ትልቁን የመንገድ ሽፋን በመያዝ የመሪነት ደረጃ ላይ ከምትገኘው ደቡብ አፍሪካ እና በ195 ሺህ ኪሎ ሜትር ሁለተኛ ደረጃን ከያዘችው ናይጄሪያ ቀጥላ እንደምትገኝ ያመለከተው ተቋሙ ኬንያ ከአህጉሪቱ አራተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧንም ጠቅሷል።
ይህ የሀገራት ምዘና አገልግሎት የሚሰጠውን አጠቃላይ የመንገድ ሽፋን የሚለካ መሆኑን የገለጸው ተቋሙ ይህም የመንገድ መሠረተ ልማት የሀገራትን ዕድገት ደረጃ፣ እንዲሁም ወደ ኢንዱስትሪ ተቋማት፣ ተርሚናሎችና ወደቦች ለመድረስ የሚያስችል ቁልፍ መስፈርት እንደሆነም ነው የገለጸው።
አክሎም የትራንስፖርት መሠረተ ልማት ለሀገራዊ እድገትና ለደኅንነት ወሳኝ እንደሆነ ገልጿል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ አሜሪካ ከ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የመንገድ ሽፋን ያላት ቀዳሚ ሀገር ስትሆን፣ ሕንድ፣ ቻይና፣ ብራዚል እና ሩሲያ በቅደም ተከተል ይከተላሉ።
