EthiopiaNews

በአዲስ አበባ 20 ተጨማሪ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ማዕከላት እንደሚከፈቱ ከንቲባ አዳነች አበቤ ተናግረዋል።

የከተማ አስተዳደሩ የቀጣይ አምስት ዓመትና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ውይይት ማጠቃለያ መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት ከንቲባ አዳነች በምርጫ ለሕዝብ የገባነውን ቃል ለመፈጸም 24/7 በትጋት በመስራት አዲስ አበባን ተምሳሌታዊ ከተማ እናደርጋታለን ብለዋል።

ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚተገበረው የመዲናዋ ስትራቴጂክ ዕቅድ ከሀገራዊ ርዕይ፣ ፖሊሲና ስትራቴጂ አንጻር የተቃኘ መሆኑን ያነሱት ከንቲባዋ በዚህም ጠንካራ የተቋም ግንባታ፣ የተቀናጀ ጥራት ያለውና ሰፊ የመሰረተ ልማት ግንባታ፣ አይበገሬ አረንጓዴ ኢኮኖሚ መፍጠር፣ የፋይናንስ አቅምን ማጠናከር እንዲሁም ዘላቂ ሰላምና ደህንነትን ማረጋገጥ ላይ ትኩረት ይደረጋል ነው ያሉት፡፡

አሁን ላይ በከተማ አስተዳደሩ 11 የመሶብ ማዕከላት መኖራቸውን ጠቁመው በ2019 በጀት ዓመት ተጨማሪ 20 ማዕከላት እንደሚከፈቱ ተናግረዋል፡፡

ማዕከላቱ የሚከፈቱት ወረዳዎችን በክላስተር በማደራጀት እንደሆነና በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት 66 መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ማዕከላትን ለመክፈት መታቀዱን አመልክተዋል።

በሁሉም ዘርፍ የተሳለጠ እና ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት ለመስጠት የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ከንቲባዋ የተናገሩት፡፡