ከ7 አመት በፊት በኢትዮጵያ በተከሰከሰው የቦይንግ አውሮፕላን አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ ኬንያዊያን መንገደኞችን የወከሉ 32 ቤተሰቦች እያንዳንዳቸው 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ሊከፈላቸው መሆኑ ተገልጿል።
ቦይንግ በአደጋው ህይወታቸውን ላጡ 9 ኢትዮጵያዊያን ካሳ መክፈሉ የሚታወስ ሲሆን አሁን በአደጋው ህይወታቸውን ላጡ ለኬንያዊያኑ ተጎጂ ቤተሰቦች በአጠቃላይ 87 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍል ፍርድ ቤት መወሰኑን የቱርኩ የዜና ወኪል አናዶሉ ዘግቧል።
ለኬንያዊያኑ ቤተሰቦች የሚከፈላቸው ካሳ፣ ቦይንግ በወንጀል ላለመከሰስ ከአንድ ዓመት በፊት ከአሜሪካ ፍትሕ መስሪያ ቤት ጋር በደረሠበት ስምምነት መሠረት ካቋቋመው የ444 ሚሊዮን ዶላር የተጎጂዎች የካሳ ፈንድ ላይ ነው ያለው ዘገባው ቦይንግ ከአደጋው ጋር በተያያዘ የቀረቡበትን የካሳ ክፍያ ክሶች 90 በመቶ ያህሉን የቋጫቸው ከፍርድ ቤት ውጭ ባሉ ድርድሮች ነው ብሏል።
ከ30 በላይ ሀገራት ዜግነት ያላቸው 157 ተሳፋሪዎችን ይዞ በኢትዮጵያ በተከሰከሰው የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን አደጋ ከሞቱት ሁሉም ተሳፋሪዎች ውስጥ 9ኙ ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ይታወሳል።
