EthiopiaNews

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የ2019 ዓ.ም ዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ የበዓል ባዛር በይፋ አስጀመረ።

ቢሮው የበዓል ባዛሮቹ በ11 ክ/ከተሞች በይፋ መጀመራቸውን ገልጿል።

የቢሮው የግብይት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ፀጋዬ ደበላ የፍጆታ አቅርቦት ችግር አለመኖሩን ገልጸው በዓልን እንደ ሰበብ በማድረግ በምርት ላይ አግባብነት የሌለው የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ፣ ምርት በሚያከማቹና በሚደብቁ ላይ መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳል ብለዋል።

አቶ ፀጋዬ አያይዘውም የዘንድሮውን የዘመን መለወጫ በዓል ምክንያት በማድረግ በተከፈቱ ባዛሮች ላይ በቂ ምርት መቅረቡን ገልፀው የከተማው ነዋሪ በባዛሮቹ ተገኝቶ እንዲገበያይ መልዕክት አስተላልፈዋል።

እንደ አቶ ፀጋዬ ገለፃ ቢሮው በየወቅቱ የሚያዘጋጃቸው የበዓል ባዛሮች በበዓል ወቅት ሊከሰት የሚችልን የዋጋ ንረት በመከላከል ገበያውን በማረጋጋት ረገድ የማይተካ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

ቢሮው የበዓል ባዛሮቹ ከትናንት ነሐሴ 28 2018 አ.ም ጀምሮ እስከ ጷግሜ 5/2018 ዓ ም ለህብረተሰብ ክፍት ሆነው አገልግሎት የሚሰጡ መሆኑን ገልጿል።መረጃው ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የተገኘ ነው።