EthiopiaNews

በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚንስትር ፍራንክ ጋርሺያ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ጋር በአቪዬሽን ዘርፍ ያለውን ግንኙነትና አየር መንገዱ ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ያለውን አጋርነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።

በቢሾፍቱ እየተገነባ የሚገኘውን ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታን የጎበኙት ረዳት ሚኒስትሩ በፕሮጀክቱ ለመሳተፍ የአሜሪካ ኩባንያዎች ፍላጎት እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡

የአሜሪካ የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን ለአውሮፕላን ማረፊያውና በአከባቢው ለሚገኙ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ብድር ለማቅረብ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ለመመደብ ማቀዱንም ፍራንክ ጋርሺያ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚንስትሩ አዲስ አበባ ቆይታቸው ከውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ ጋር የኢትዮጵያና አሜሪካን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ መምከራቸው የሚታወስ ነው፡፡

የሁለቱ ባለሥልጣናት ውይይት፣ በቀጠናዊ ሰላምና ጸጥታ ላይ ጭምር ያተኮረ እንደነበር የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ገልጿል፡፡