EthiopiaNews

ለ 10 ዓመታት ኤሌክትሪክ ሳያገኙ የቆዩ 5 ሺህ አዲስ ደንበኞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ ተገልጿል።

የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ የሆኑት በኦሮሚያ ክልል በአምስት ዞኖች የሚገኙ ምስራቅ ጉጂ፣ ጉጂ፣ ምዕራብ አርሲ፣ ቦረና እና ምስራቅ ቦረና ዞኖች የሚገኙ ደንበኞች ናቸው ተብሏል።

ከእነዚህ መካከል በጉጂ ዞን ኦዶ ሻኪሶ ወረዳ እንዲሁም በቦረና ዞን ተልተሌ ወረዳ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚገኙበት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አሳውቋል።

በተጨማሪም በአካባቢዎቹ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ተቋማት፣ ፖሊስ ጣቢያዎች እና የማዘጋጃ ቤት ቢሮዎችን ጨምሮ በርካታ ማህበራዊና የመንግስት ተቋማት የኤሌክትሪክ ሃይል ማግኘት ችለዋል ነው ያለው።

ቀደም ሲል በአካባቢዎቹ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ባለመኖሩ ነዋሪዎች በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎቻቸው ላይ ከፍተኛ ጫና እና እንግልት ይደርስባቸው ነበር ያለው አገልግሎቱ ከዋናው ግሪድ ርቀው የሚገኙ የገጠር ከተሞችንና ቀበሌዎችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚስችሉ የሶላር ሚኒ ግሪድ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ ወደ ስራ መግባቱንም አክሎ ገልጿል፡፡

ተቋሙ በአውሮፓውያኑ በ2030 ከዋናው ግሪድ 65 በመቶ እንዲሁም በአማራጭ የኃይል ምንጮች 35 በመቶ የሚሆነውን ህብረተሰብ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝም ነው ያስረዳው፡፡

#EBS
#EBSTVNEWS
#_7696_WN
https://t.me/ebstvnews
www.ebstv.tv