ባለፉት 3 ዓመታት ህብረተሰቡን በማሳተፍ በተሰበሰበ 146 ቢሊዮን ብር ወጪ ከ17 ሺህ በላይ አዳዲስ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አስታወቁ።
ሚኒስትሩ አክለውም ከ36 ሺህ በላይ የሚሆኑ ነባር ትምህርት ቤቶችም እድሳት እንደተደረገላቸው ገልጸው ከዚሁ ጋር ተያይዞ የቅድመ-መደበኛ ትምህርት ቤቶች ቁጥር ከነበረበት 4 ሺህ ወደ 36 ሺህ ከፍ ማለቱን ጠቁመዋል።
ከትምህርት መሣሪያዎችና ከአቅም ግንባታ አንጻርም ከተካሄደው የስርዓተ-ትምህርት ማሻሻያ ከ45 ሚሊዮን በላይ የሁለተኛ ደረጃ መማሪያ መጻሕፍት ታትመው ለተማሪዎች መዳረሳቸው ሲገለጽ ከ120 ሺህ እስከ 130 ሺህ የሚጠጉ መምህራንም በዘመናዊ የሥልጠና አሰጣጥ ዘዴዎች አቅማቸውን የሚያሳድግ ስልጠና እንዲያገኙ መደረጉን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
