በአዲስ አበባ በብልሽት ምክንያት የተለያዩ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጡ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአዲስ ዌስት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ ባጋጠመ ድንገተኛ የትራንስፎርመር ብልሽት ምክንያት በተለያዩ የመዲናዋ ክፍሎች የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጡን ገልጿል።
በዚህ ሳቢያ በአውቶብስ ተራ፣ አዲስ ከተማ፣ መሳለሚያ፣ አማኑኤል፣ ሰባተኛ፣ ኮልፌ፣ ቀራንዮ፣ ቤተል፣ ጦር ኃይሎች፣ ወይራ ሰፈር እና አካባቢዎቻቸው የሚገኙ በርካታ የመኖሪያ፣ የንግድና የማህበራዊ አገልግሎት ተቋማት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋርጦባቸዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የጥገና ባለሙያዎች ብልሽቱን በፍጥነት በማስተካከል አገልግሎቱን ወደ ነበረበት ለመመለስ በትክክል እየሰሩ መሆኑ ተገልጿል።
ተቋሙ የጥገና ሥራው እስከሚጠናቀቅ ደንበኞች በትዕግሥት እንዲጠባበቁ እየጠየቀ ተጨማሪ መረጃዎችን በይፋዊ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾቹ እንደሚያሳውቅ ገልጿል።
