የደቡብ ኮሪያው ተሽከርካሪ አምራች ኩባንያ ኬጂ ሞቢሊቲ በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ፋብሪካ ሊገነባ መሆኑን አስታወቀ፡፡
መገጣጠምያውን ለማቋቋም ከኢትዮጵያው ቢ.ኤንድ.ሲ ማኑፋክቸሪንግ ግሩፕ እና ከየንግሳን ግሎኔት ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሙን ያስታወቀው ኬጂ ሞቢሊቲ የሚገጣጥማቸውን ተሽከርካሪዎች ወደ ተለያዩ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት የመላክ እቅድ እንዳለውም ገልጿል፡፡
ግንባታውን በመጪው ጥቅምት ወር በመጀመር በፈረንጆቹ 2027 አጋማሽ ማምረት ለመጀመር የታቀደ ሲሆን፣ የተለያዩ ሞዴል ያላቸውን 1 ሺህ ገደማ ተሽከርካሪዎችን በዓመት ለመገጣጠም እቅድ መያዙንም በደቡብ ኮሪያ የሚገኘው ሴኦል ኢኮኖሚክ ዴይሊ ዘግቧል።
በስምምነቱ መሠረት ቢኤንድሲ መሠረተ ልማት በማመቻቸት ግንባታውን የሚቆጣጠር ሲሆን፣ የንግሳን ግሎኔት ደግሞ የፋብሪካ ዲዛይን፣ የቴክኒክ ማማከር እና የማምረቻ መሣሪያዎችን እንደሚያቀርብ እንዲሁም ኬጂ ሞቢሊቲ ደግሞ ለተሽከርካሪ መገጣጠሚያነት የሚያገለግሉ እቃዎችን እንደሚያቀርብ ዘገባው ጠቅሷል፡፡
