EthiopiaNews

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ለሚገኙ የክርስትና እምነት ተከታዮችና ለበአሉ ተካፋዮች በሙሉ እንኳን ለ2019 ዓመተ ምህረት ብርሃነ መስቀሉ እና ደመራ በዓል በሰላም እና በጤና አደረሳችሁ ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

ጉባኤው በየዓመቱ መስከረም 16 እና 17 ቀናት የሚከበረው የደመራና የመስቀል በዓል፣ ከታሪካዊና መንፈሳዊ ፋይዳው ባሻገር ሕዝባችን በአብሮነት፣ በፍቅርና በሰላም እንዲኖር ያስቻለ ታላቅ ሀገራዊና ሃይማኖታዊ እሴት ነው ብሏል፡፡

የደመራ መብራት ከሩቅ ሲታይ የሁሉንም አይን እንደሚስብ፣ የዚህ በዓል መከበርም የኛን ልብ በአንድነት፣ አብሮነት ያጠናክራል ያለው ጉባኤው በዓሉ ጎረቤት ከጎረቤት፣ ዘመድ ከዘመድ ጋር የሚገናኝበት፣ የተጣላ የሚታረቅበት እና የደስታ መካፈያ ትልቅ መድረክ እንደሆነም ነው ያስታወቀው።

አክሎም የመስቀል እና ደመራ በዓልን ስናከብር አቅመ ደካሞችን፣ የተሰደዱትንና ችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችን በመርዳትና በመተጋገዝ እንደ ደመራው በጋራ በመሆን የእግዚአብሔርን ፍቅር በተግባር በማሳየት እንዲሆን የአክብሮት ጥሪ አቀርባለሁ ብሏል ጉባኤው በጠቅላይ ጸኃፊው ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በኩል ባወጣው መግለጫ፡፡