የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት 19ኛው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን በመጪው ሰኞ ጥቅምት 2 ቀን 2019 ዓ.ም እንደሚከበር አስታወቀ፡፡
19ኛው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን “ሠንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባትና ለአንድነታችን” በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር ነው የተገለፀው።
በምክር ቤቱ ከጠዋቱ 3 ሰአት ጀምሮ በሚኖረው አከባበር ላይ የሚገኙት ርዕሰ ብሔር ታዬ አፅቀስላሴ ዕለቱን አስመልክቶ ለመላው ኢትዮጵያውያን መልዕክት በማስተላለፍ በንግግር እንደሚከፍቱም ተጠቁሟል፡፡
እንዲሁም በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት አማካኝነት በቀጥታ ስርጭት በመላው ሀገሪቱ ዜጎች በሠንደቅ ዓላማው ፊት ቃለ መሃላ የሚፈጸምበት ሥነ ሥርዓት ይፈጸማል ተብሏል፡፡
ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን መከበር ከጀመረ አስራ ስምንት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን ዘንድሮ ለአስራ ዘጠነኛ ጊዜ በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት መሪነትና አስተባባሪነት በመላ ሀገሪቱ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል፡፡
ይህ በዓል በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ በውጭ ሀገር በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንስላዎች በተመሳሳይ ሰዓትና ድምቀት ይከበራል።
መረጃው ከሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የተገኘ ነው።
