የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ደንብን መተግበር የሚያስችል ረቂቅ መመሪያ መዘጋጀቱ ተገለጸ፡፡
መመሪያው የኢንቨስትመንት ማበረታቻውን በብቃት ለመተግበር፣ የመንግስትን የፊስካል ጥቅም የሚያስጠብቅና ግልጽ አሰራር ለመዘርጋት እንዲሁም ለልማት የሚሰጡ ማበረታቻዎችን በአንድ ቋት ለማጠቃለል ያለመ እንደሆነ ተገልጻል።
ረቂቅ መምሪያውም የቁጥጥር ስርዓትና የተጠያቂነት አሰራር ከመዘርጋት ባለፈ ባለሃብቶች ማበረታቻውን ከመጠቀማቸው በፊት የአፈጻጸም ስምምነት እንዲፈርሙ የሚያደርግ፣ ለእያንዳንዱ ፕሮጀክት የተለየ የሂሳብ መዝገብ መያዝን የሚያስገድድ፣ አመታዊ ሪፖርት የማቅረብና ከቀረጥ ነጻ የገባውን እቃ ለታለመለት አላማ ብቻ የመጠቀም ግዴታን የሚጥል ነው።
ግዴታቸውን ባልተወጡና ጥፋት በፈጸሙ አካላት ላይም እርምጃ እንዲወሰድ የሚያደርግ መሆኑ ነው የገንዘብ ሚኒስቴር በረቂቅ መመሪያው ላይ በተደረገው ምክክር ላይ የገለጸው፡፡
ዋነኛ ዓላማውም ውጤታማ ያልሆኑ የታክስ ማበረታቻዎችን በማስቀረት የታክስ ወጪን መቀነስ፣ የመንግስት ገቢን ማሻሻልና የሚሰበሰበውን ገቢ ለመሰረተ ልማት በማዋል ለኢንቨስትመንት ይበልጥ ምቹ አካባቢን መፍጠር ነው ተብሏል፡፡
