EthiopiaNews

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሠንደቅ ዓላማችን የጋራ ታሪካችንን፣ ሉዓላዊነታችንና በልዩነቶቻችን መካከል በጋራ የመቆም አቅማችንን የሚያስታውስ የብሔራዊ አንድነታችን ምልክት መሆኑን ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄን ያሉት 19ኛውን ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን አስመልክቶ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ነው።

በዓድዋ የሀገሪቱ ሕዝቦች ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን በመተው በጋራ በመቆማቸው፣ በታላቅ ገድላቸው የዓለምን ትኩረት መሳብ ችለዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አባቶቻችን በፈተናዎች ከመከፋፈል ይልቅ አንድነታቸውን አሳይተዋል ሲሉም ገልጸዋል።

ይህ በጋራ የመቆም ጥሪ መቼም ቢሆን ተቋርጦ አያውቅም፤ እያንዳንዱም ትውልድ ለዚህ ጥሪ እንዴት ምላሽ መስጠት እንዳለበት ጠንቅቆ ያውቃል ብለዋል።

ቋንቋዎቻችን፣ ሃይማኖቶቻችን እና ማንነቶቻችን ለዘመናት በጋራ በምናልፍበት ታሪካዊ ጉዞ ውስጥ አብረው ተሰናስለው የተሸመኑ የአንድ ሸማ ክሮች ናቸው ብለዋል።

ለሀገር መቆም ከትንንሽ የድፍረት እርምጃዎች ይጀምራል፤ ከራስ አልፎ ሰፊ ርዕይ ይዞ መሥራትንም ይጠይቃል ሲሉም ገልጸዋል።

ያለፉት ትውልዶች ሀገሪቱን እንድንረከብ መስዋዕትነት ከፍለዋል፤ ዛሬ በጋራ የምናጸናትን ሀገር ነው ለቀጣዩ ትውልድ የምናስተላልፈው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‎ስለሆነም ዛሬ ራስዎን ይጠይቁ፤ ለሀገርዎ አንድነትና ብልጽግና ምን አበረክታለሁ? ብለው እንዲጠይቁም መልዕክት አስተላልፈዋል።