የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የሸማቾች ማኅበራት የምርት አቅርቦትና ጥራት እንዲያድግ ተጨማሪ 500 ሚሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ መመደቡን ተናገሩ።
ከንቲባዋ ይሄን ያሉት ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪን ለመቆጣጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር ባካሄዱት ውይይት ላይ ነው።
በመዲናዋ በመሠረታዊ የዕለት ተዕለት ፍጆታዎችና በቤት ኪራይ ላይ እየታዩ ያሉ ምክንያታዊ ያልሆኑ የዋጋ ጭማሪዎችን ለመቆጣጠርና የዜጎችን የኑሮ ጫና ለማቃለል እየተወሰዱ ባሉ የአጭርና የረጅም ጊዜ መፍትሔዎች ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።
ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታትና ፍትሐዊ የገበያ ሥርዓትን ለማረጋገጥም ከተማ አስተዳደሩ ዋና ዋና እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝ ከንቲባዋ ገልፀዋል።
ከተማ አስተዳደሩ እየወሰዳቸው ካላቸው እርምጃዎች መካከል የመጀመሪያው የምርት አቅርቦትን ማሳደግ ሲሆን፣ የመሠረታዊ ፍጆታ ምርቶችን አቅርቦት በመጨመር የዋጋ መረጋጋትን ለማምጣትና ሸማቹ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ሁኔታዎች እንደሚመቻቹ ተናግረዋል።
የገበያ ማዕከላትን ማስፋፋትና የደላላ ሰንሰለትን ማሳጠር ትኩረት የተሰጠው ሲሆን፣ አምራቾችንና ሸማቾችን በቀጥታ የሚያገናኙ የገበያ ማዕከላትን በከተማዋ መግቢያ በሮች ላይ በማቋቋም ምርቶች በቀጥታ ለሸማቾች እንዲቀርቡ እየተሠራ እንደሚገኝ ነው ከንቲባዋ የገለጹት።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ ጠንካራ የሕግ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልፀዋል።
የገበያ ሥርዓትን በሚጥሱና ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ የቁጥጥርና የሕግ ማስከበር ሥራው ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ከንቲባዋ ተናግረዋል።
