EthiopiaNews

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በጥቅምት ወር የሚካሄደውን ምልዐተ ጉባኤ ዛሬ ጀምሯል።

ቅዱስ ሲኖዶሱ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚካሂደው ምልዓተ ጉባኤ አካል የሆነው ይህ ጉባኤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቡራኬ ተከፍቷል።

ጉባኤው ለቤተ ክርስቲያኗ ጠቃሚ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በተለይም በአንዳንድ አህጉረ ስብከት የሚታዩ የአሠራር ክፍተቶችን ማረም፣ የምእመናን አያያዝ እንዲሁም ሐዋርያዊ ተልእኮን በተገቢው ሁኔታ መፈጸም ላይ ውይይት ያደርግባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ቅዱስ ሲኖዶሱ በተለያዩ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይም ትኩረት ያደርጋል የተባለ ሲሆን ሰላምን ለማስፈን በሚደረግ ጥረት ሁሉ ከባለድርሻ አካላት ጋር መስራት በሚገባው ጉዳይ ላይ ውይይት እንደሚያደርግም ተገልጿል።

ጉባዔው ብጹኣን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና የቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት በተገኙበት ተጀምሯል፡፡