InternationalNews

ኢትዮጵያ ከካናዳ ጋር በዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ማዕቀፍ ውስጥ የሁለትዮሽ የገበያ መዳረሻ ፕሮቶኮል ማፅደቋን የሚያሳይ የታሪክ ምዕራፍ የሆነ ስምምነት በጄኔቫ በሚገኘው የዓለም የንግድ ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት ተፈረመ።

ይህ ስምምነት የሁለቱን ሀገራት የ6 አስርት ዓመታት አጋርነት የሚያጠናክርና ኢትዮጵያ ወደ ዓለም የንግድ ድርጅት የምታደርገውን ጉዞ የሚያፋጥን ትልቅ ምዕራፍ መሆኑ ተገልጿል።

በስምምነት ስነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት በጄኔቫ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይ አምባሳደር ጸጋአብ ክበበዉ ስምምነቱ የንግድ ግንኙነትን ከማስፋት ባለፈ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ወዳጅነት የሚያረጋግጥ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ሀገሪቱ የምታደርጋቸው ማክሮ ኢኮኖሚያዊ እና መዋቅራዊ ማሻሻያዎች አንዱ ዋና ምሰሶ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ከካናዳ ጋር የተደረገው ይህ የሁለትዮሽ ስምምነትም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በማዕድን፣ በታዳሽ ሃይል እና በሎጂስቲክስ ዘርፎች ሰፊ የንግድና የኢንቨስትመንት ትስስር ለመፍጠር ትልቅ መሠረት የሚጥል ነው።

ይህ የሁለትዮሽ የገበያ መዳረሻ ስምምነት መፈረም ኢትዮጵያ ከካናዳ ጋር የነበራትን የንግድ ድርድር በስኬት ማጠናቀቋን የሚያሳይና በቀጣይ ከኖቨምበር 9–10, 2026 ለሚካሄደው 8ተኛው የኢትዮጵያ የንግድ ድርድር የስራ ቡድን ስብሰባ አብይ ዝግጅት መሆኑ ተገልጿል።