EthiopiaNews

በኢትዮጵያ ከ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ክፍት የመንግሥት የሥራ መደቦች ባሉበት ሁኔታ፣ ምንም ዓይነት ሠራተኞችን የመቀነስ ዕቅድ አለመኖሩን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ በአሁኑ ወቅት እየተተገበረ ያለው አጠቃላይ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ዋና ዓላማ ሠራተኞችን መቀነስ ሳይሆን በተመደቡበት የሥራ ዘርፍ ብቃታቸውን፣ ክህሎታቸውንና አገልግሎት የመስጠት አፈጻጸማቸውን ማሳደግ ነው ብለዋል።

አዲሱ የመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ የመንግሥት ሠራተኞች ይቀነሳሉ የሚሉ የተሳሳቱ መረጃዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ሲሰራጩ እንደነበር ኮሚሽነሩ አስታውሰው እነዚህ ወሬዎች የሪፎርሙን አገራዊ ዓላማና ተቋማዊ ይዘት በትክክል የማያሳዩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

እንዲሁም በፌዴራልና በክልል ደረጃ የመንግሥት የሥራ መደቦችን የመረጃ የማጥራትና የማደራጀት ሥራ በተግባር ተከናውኖ ከ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የሥራ መደቦች መኖራቸው መለየቱ ሲነገር ከእነዚህ ወደ 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚጠጉት ብቻ በሠራተኞች የተያዙ ናቸው ተብሏል።

ኢትዮጵያ ካላት እያደገ ከመጣ የሕዝብ ብዛትና የአገልግሎት ፍላጎት አንጻር ተጨማሪ የመንግሥት ሠራተኞች የሚያስፈልጓት መሆኑን በግልጽ የሚያመለክት ነው የተባለ ሲሆን በኢትዮጵያ የሲቪል ሰርቪስ ዘርፍ ውስጥ የሰው ኃይል በትርፍ መጠን አለ የሚል ጥናትም ሆነ ድምዳሜ አለመኖሩም ተጠቁሟል።