የጤና ሚኒስቴር የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት እና የቤልጂየሙ አንትወርፕ ትሮፒካል ሜዲሲን ኢንስቲትዩት በጋራ ያዘጋጁት ዓለም አቀፍ ሳይንሳዊ ጉባኤ መካሔድ መጀመሩን አስታወቀ።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በሽታ አምጪ ተሕዋስያን ድንበር እንደማይገድባቸው ጠቅሰው በዓለም አቀፍ የጤና ደንቦች፣ በኢጋድ የመረጃ ልውውጥ ማዕቀፎች እና በአፍሪካ መድኃኒቶች ኤጀንሲ በኩል ክልላዊ ትብብር እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ሚኒስትሯ ጉባኤውም የዕውቀት ሉዓላዊነት መገለጫ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የቤልጂየም አምባሳደር ዶ/ር አንኤሊስ ቨርስትሼል በበኩላቸዉ ኢትዮጵያ ምርምርንና ፖሊሲን በማስተሳሰር ረገድ ምሳሌ መሆኗን ጠቅሰው ቤልጂየም ሀገራዊ ምርምሮችን ወደ ዓለም አቀፍ አጀንዳ ለማምጣት በአጋርነት እንደምትሰራ አረጋግጠዋል።
የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ዶ/ር ዓለምሰገድ አብዲሳ ሳይንስና ምርምር የሚገባቸውን ማህበረሰቦች በውጤታማነት መድረስ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ጉባኤው ሳይንሳዊ ግኝቶችን ወደ ተጨባጭ ፖሊሲ ለመቀየር ዘላቂ አጋርነትን እንደሚፈጥርና ከቤልጂየሙ አንትወርፕ ትሮፒካል ሜዲሲን ኢንስቲትዩት ጋር ለሚደረጉ የጋራ ምርምሮች አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍት ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በጉባኤው ዓለም አቀፍ ተመራማሪዎች፣ የሕብረተሰብ ጤና ባለሙያዎች እና ፖሊሲ አውጪዎች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተገልጿል።
በሰዎች፣ በተህዋሲያን፣ በአስተላላፊዎች ፣ በአካባቢ ጥበቃ እና በፖሊሲዎች እንቅስቃሴ ምክንያት በሚፈጠር የተላላፊ በሽታዎች ሥርጭትና የጤና ሥርዓቶች የመቋቋም አቅም ላይ ጉባኤው እንደሚመክር የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።
