የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በምታስተናግደው የኮፕ 32 ጉባኤ ሁሉም ሀገራት ፍትሃዊ እድል እንዲያገኙ በቁርጠኝነት እንደምትሰራ ተናገሩ።
31ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 31) በቱርክ አንታሊያ መካሄዱን ቀጥሏል።
ከጉባኤው ጎን ለጎን ሁለተኛውን ዓለም አቀፍ የጋራ ግምገማ ይፋ ለማድረግ የተዘጋጀ የሚኒስትሮች ከፍተኛ ደረጃ ውይይት ተካሄዷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የኮፕ 32 ተመራጭ ፕሬዚዳንት ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በውይይቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ትብብርን ለማጠናከር ያለመውን የኢትዮጵያን ርዕይ አብራርተዋል።
ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የጋራ ግምገማ፣ በጋራ የተመዘገበውን እድገት በግልጽ ሁኔታ መገምገም፣ የአፈጻጸም እንቅፋቶችን መለየት፣ እንዲሁም የአየር ንብረት እርምጃዎችንና ድጋፎችን ለማፋጠን የሚያስችሉ አማራጮችን ማመላከት እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።
በአዲስ አበባ በሚካሄደው የኮፕ 32 ጉባኤ ይህንን ሥራ ወደፊት ለማስቀጠልና ሁሉም ሀገራት ትርጉም ያለው ድምፅ እንዲኖራቸውና የድርሻቸውን ለመወጣት ፍትሐዊ ዕድል እንዲያገኙ ኢትዮጵያ ያላትን ቁርጠኝነት ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
