EthiopiaNews

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ ከህዳር 14 እስከ 18 ቀን 2019 ዓ.ም የሚካሄደው 5ኛው የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤን እንደምታስተናግድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄን ያሉት በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባጋሩት የቪዲዮ መልእክት ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉባኤው ለሚሳተፉ ሚኒስትሮች ፣ የልማት አጋሮች እና ሌሎችም ለማስተናገድ ዝግጁ ነን ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጋራ በመሆን፣ የጋራ መሻቶቻችንን ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንቀይር፤ የበለጠ ጤናማ እና ተግዳሮቶችን መቋቋም የምትችል አፍሪካን እንገንባ ብለዋል።

ጉባዔው በአፍሪካ የጤና ትብብሮች እንዲጠናከሩ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
ጉባኤው በኢትዮጵያ መንግሥትና በአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ አፍሪካ ሲዲሲ በጋራ የሚዘጋጅ ሲሆን ከ30 ሺህ በላይ ተሳታፊዎችን ያስተናግዳል ተብሎ ይጠበቃል።

የዘንድሮው ጉባኤም አፍሪካ በጤና ዘርፍ በውጭ ድጋፍና አቅርቦት ላይ ያላትን ጥገኝነት በመቀነስ፣ በራሷ ሀብት፣ እውቀት፣ ቴክኖሎጂና የምርት አቅም የሕዝቦቿን ጤና የምትጠብቅበትን ሥርዓት እንድትገነባ ያበረታታል።

የጉባኤው ዋነኛ ዓላማ የአፍሪካ ሀገራት የጤና ችግሮቻቸውን በጋራ እንዲመረምሩ፣ የተሳኩ ልምዶችን እንዲለዋወጡና ተግባራዊ መፍትሔዎችን እንዲያዘጋጁ ዕድል መፍጠር ሲሆን በጉባኤው የፖሊሲ አውጪዎች፣ ተመራማሪዎች፣ የጤና እና የቴክኖሎጂ ባለሙያዎችና የግሉ ዘርፍ ተወካዮች በአንድ መድረክ በመገናኘት በአህጉሪቱ የጤና ዘርፍ ያሉ ተግዳሮቶች ላይ ይወያያሉ።

መረጃው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የማህበራዊ የትስስር ገፅ እና ከአፍሪካ ሲዲሲ የተገኘ ነው።