EthiopiaNews

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለፀሐይ ተጋልጠው የሚሸጡ የምግብና መጠጥ ምርቶችን እንዲሁም ሕገ-ወጥ የትምባሆ ዝውውርን ለመቆጣጠር እንደሚሰራ ገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን፣ የከተማዋ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ እንዲሁም ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን በከተማዋ ሕገ-ወጥ የንግድ አሰራሮችን በመቆጣጠር የሕዝብ ጤና ለመጠበቅ የሚያስችል ስምምነት ባደረጉበት ወቅት ነው ይህን የገለጹት፡፡

በስምምነቱ መሰረት ሦስቱ ተቋማት በጋራ በሚያቋቁሙት ግብረ-ኃይል አማካኝነት ለፀሐይ ተጋልጠው የሚሸጡ የታሸጉ ምግቦችን፣ መጠጦችንና የሕፃናት ወተቶችን የመውረስና የማስወገድ እርምጃ እንደሚወስዱ የተገለጸ ሲሆን ሕብረተሰቡም እነዚህን ለጸሃይና ሌሎች አደጋዎች የተጋለጡ ምርቶችን ባለመግዛት እንዲተባበር ጥሪ ቀርቧል።

ተገቢ ባልሆነ መንገድ ለፀሐይ ተጋልጠው የሚቀመጡ ምርቶችን መጠቀም በከተማዋ እየተበራከቱ ለመጡት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መንስኤ መሆናቸውም በስምምነቱ ወቅት ተጠቅሷል፡፡